Asset Publisher Asset Publisher

Back

ባቴክኖሎጂ ለኢትዮጵያ ቅንጦት አይደለም!!

የአንድን ሃገር መጻይ ጊዜ ብሩህ ለማድረግ እጅጉን አስፈላጊ የሆነና የበለጸጉ ሃገሮች በከፍተኛ ፍጥነት ወደ ቀጣይ
የቴክኖሎጂ መዘውሮች የተሸጋገሩበት ቴክኖሎጂ መሆኑን ልብ ማለት ይሻል፡፡ ይህ ቴክኖሎጂ ባዮቴክኖሎጂ ይባላል፡፡ ታዲያ
ቴክኖሎጂው ምንድነው ለሃገራችንስ ምን ፋይዳ አለው?
 
ብዙዎች ባዮቴክኖሎጂ በተለይም የግብርና ባዮቴክኖሎጂ ሲባል የዘረ-መል ምህንድስና ጉዳይ ብቻ የሚመስለን እንዳለን
በተለያየ ጊዜ ባደረኩት ምልከታ ማረጋገጥ ችያለሁ፡፡ በዚህም ስለቴክኖሎጂው አስፈላጊነት ገብቷቸው የሚመክሩ እንዳሉ
ሁሉ ሳይገባቸው በአያስፈልግም ስሌት የሚከራከሩ እንዳሉ ይስተዋላል፡፡
ነገር ግን ባዮቴክኖሎጂ የዘረ-መል ምህንድስና (genetic engineering) ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም ዘረ-
መል ምህንድስና ባዮቴክኖሎጂ ከሚስራቸው ዘርፈ ብዙ ስራዎች አንድ ክፍል (ቅንጣት) እንጂ፡፡ የሰውን ልጅ የኑሮ ደረጃ
ወደተሻለ ሁናቴ የሚያሸጋግሩ ለምሳሌ ያክል፡- በጤና ባዮቴክኖሎጂ የሰውን ልጅ ህይወት የሚታደጉ መደሃኒቶችን፣
መመርመሪያ መሳሪያዎችና የበሽታ መለያ መመርመሪያ ዘዴዎች የመፍጠር፤ በግብርናው ምርትና ምርታማነትን መጨመር
፤ በኢንዱስትሪ አዳዲስ ነገረ ጉዳዮችን የመፍጠር፤ የአካባቢን ደህንነትን በመጠበቅ ላይ ትኩረት በማድረግ የሰው ልጆችን
መሰረታዊ ፍላጎቶች ለሟሟላት የሚገለግል ቴክኖሎጂ ነው፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እ.ኤ.አ በ1992 ብራዚል ላይ ባካሄደው የብዝሃ ህይወት (Earth summit)
ኮንፈረንስ የባዮቴክኖሎጂ ትርጓሜን እንዳስቀመጠው ባዮቴክኖጂ ማለት ‟ማንኛውንም ስነ-ህይወታዊ ስርዓቶችን ፣
ህይዎት ያላቸው ነገሮችን እና ከነዚህ የሚገኙ ማንኛውንም ነገሮችን በመጠቀም የተለያዩ ምርቶችን ማምረትና ማሻሻል
ወይም የአሰራር ዘዴዎችን በመፍጠር ለተወሰነ ጥቅም ማዋል ማለት ነው፡፡″
ባዮቴክኖሎጂ በባይዎሎጂ፣በኢንጅነሪንግ፣ በኬሚስትሪና በሌሎችም የሳይንስ ዘርፎች ጥምረት የተለያዩ ህይወት ያላቸው
ነገሮችን በልዩ ልዩ ቤተ-ሙከራ ዘዴዎች በመጠቀም የተለያዩ ሥነ-ህይወታዊ ወይም ባዮኬሚካላዊ ሂደቶችን
በማሻሻል የሰው ልጅ ፍላጎት ለማሟላት የሚያስችሉ ተግባራትን የሚሰራ ሳይንስ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ሰፊ የተፈጥሮ ኃብትና የልማት ፀጋ ያላት ሃገር ናት ፡፡ ይህም በግብርና ዘርፍ የተትረፈረፈና ጥራት ያለው ምርት
ለማምረት፣ የጤና አገልግሎቶችን ለማዘመን፣ ለሰዎች ምቹ የመኖሪያ አካባቢን ለመፍጠር እና በኢንዱስትሪው ዘርፍ
አዳዲስ ነገሮችን ለማምረት የሚያስችል ሲሆን ለውጤታማነቱ የባዮቴክኖሎጂ ልማት የሚያማልል አመቺ ሁኔታን
ከመፍጠሩም ባሻገር ቁልፍ አጋዥ አቅም እንደሆነም ይታመናል፡፡
በአለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያ የበርካታ ሰብሎች ለምሳሌ፡- የኑግ፣ ጤፍ፣ ጎመንዘር፣ ቡና፣ እንሰትና እንዲሁም ሌሎች
ጥቂት አገሮች የሚጋሩዋቸው ገብስ፣ ማሽላ፣ ዳጉሳን ጨምሮ ቅድመ-መገኛ ስትሆን የመኮሮኒ ስንዴ፣ ተልባ፣ ባቄላ፣
አተር፣ ሽምብራ፣ ምስር፣ አብሽ፣ ጓያ ከፍተኛ የብዝሃ-ህይወት ተለያይነት ሁለተኛ ማዕከል ሆና ትታወቃለች።
 
ሃገራችን በጥናት ያልተለዩ በርካታ የጄኔቲክ ሃብት (በእንስሳት፣ በእጽዋት ና በደቂቅ ዘ አካላት) እንዳላት ታሳቢ ሲሆን
ይህ ኃብት በሳይንሳዊ መንገድ በሚፈለገው ደረጃ ተፈትሾ በአግባቡ ስለማይታወቁም ሃገራችን ለረጅም ዘመን በአግባቡ
ተጠቃሚ ሳትሆን ቀርታለች፡፡
የሃገራችንን የልማት ድህነት አንዳንዶች በእምቅ የጄኔቲክ ሃብት መሃል የተፈጠረ ድህነት ወይም "poverty amidst
genetic plenty" በማለት የማይመስል ግን ሊሆን የቻለ ክስተት አርገው አስገራሚነቱን ይናገራለ። ይህም በራሳችን
ኃብት ከእኛ ይልቅ ዋና ተጠቃሚ እየሆኑ ያሉት በቴክኖልጂ ያደጉ አገሮች እንደሆኑ ስለሚታወቅ ነው። በርካታ የጄኔቲክ
ኃብቶቻችን የእኛን የምርት ውጤታማነት ለማላቅ ሳይጠቅሙ ለሌው አለም የልማት ስኬታማነት አስተዋጾ ያደረጉ
ለምሳሌ፡- ቡና፣ ገብስ፣ ስንዴና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጤፍ በመሳሰሉት እየታየ ያለውን ክስተት በጥቂቱ መጥቀስ በቂ
ነው።
ታዲያ ይህ ሁሉ የተፈጥሮ ሃብት እያለ እንዴት በሃገረ አትዮጵያ የምግብ ችግር ያጋጥማል ብትሉ መልሱ የኢትዮጵያ ግብርና
ከጥንታዊ የአሰራር ስርአት ስላልተላቀቀ የሚል ይሆናል፡፡ የአለም ሃገራት በትንሽ መሬትና ብዝሃ ህይወት ባዮቴክኖሎጂን
ተጠቀመው በቂ እና ከበቂ በላይ ምርቶችን በማምረት ከራሳቸው አልፎ ለሌሎች ሲመግቡ ይታያል፡፡ ባዮቴክኖሎጂ
በግብርና፣ በጤና፣ በአካባቢና በኢንዱስትሪ ዘርፍ እየተገለገሉ የሚገኙ የአለም ሃገራት የሃገራቸው ሁለንተናዊ ብልጽግና
ወደተሻለ ደረጃ አሸጋግረውበታል፡፡
የሰው ልጅ መሰረታዊ ፍላጎት ከሆኑት የመኖሪያ ቤት፣ የምግብ፣ የአልባሳት፣ የሀይል፣ የመጓጓዣ፣ የህክምና እና
የመሳሰሉት ዛሬ ላይ ዋጋቸው አስደንጋጭ በሚባል ሁኔታ አየጨመረ ይገኛል፡፡ ለአብነት ያህል የአለማችን የሀይል ፍላጎት
በየአመቱ በ1.7% እድገት እያሳየ ነው፡፡ የህዝብ ቁጥር ከግብርናው ዘርፍ እድገትና መስጠት ከሚችለው ምርት አቅም
በራቀ ፍጥነት እየጨመረ በመምጣት በ100 አመት ውስጥ በ4 እጥፍ አድጓል፡፡ በ2050 እ.ኤ.አ 9.3 ቢለዮን
ይደርሳል ተብሎም ይገመታል፡፡ ከ20% ያላነሰው የአለማችን ህዝብ በከፍተኛ ድህነት ውስጥ ይገኛል፡፡ በርካታ የአለማችን
ህዝብ የንፁህ መጠጥ ዉሃ እንኳን አያገኝም፡፡ እነዚህ ችግሮች ደግሞ ከዚህ በፊት እንደነበረው በተፈጥሮ ሀብት ላይ
በመንተራስና ያንኑ በመመንዘር መመለስ የማይታሰብ ነው፡፡
በመሆኑም እንደ ባዮቴክኖሎጂ ያሉ የምግብ ፣ የጤና፣ የአልባሳት ፣ የአካባቢንና ለሰውልጅ አስፈላጊ የሆኑ ነገረ-
ጉዳዮችን ዋስትና የሚረጋግጡ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ቅንጦት ሳይሆን ለነገ የማይባል ጉዳይ ነው፡፡
በአለማችን እንደ ህንድ፣ ኮርያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ብራዚል ኩባ ያሉ ሃገራት ለባዮቴክኖሎጂ መስኮች ከፍተኛ ትኩረት
በመስጠታቸው የህዝባቸውን የምግብ እና ጤና ዋስትና ከማረጋገጥ ባሻገር አካባቢያቸውን ለሰው ልጆች መኖርያ ምቹ
ማድረግ ችለዋል፡፡
በሃገራችን ዛሬም በሚሉዮን የሚቆጠሩ ዜጎቻችን የምግብ ድጎማ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር የሃገራችንን ከፍተኛ
የህዝብ ቁጥርን የሚይዘው ወጣትና አሁን ካለው የህዝብ ቁጥር የመጨመር እድሉ ከፍተኛ በሆነበት ሁኔታ
ግብርናውንም ሆነ ሌሎች ለሰው ልጅ አስፈላጊ የሆኑ ጤና እና መሰል ችግሮች ለመፍታት በባዮቴክኖሎጂ በመታገዝ
ምርትና ምርታማነትን ማሻሻል እና ውጤታማነት ማረጋገጥ ለነገ የማይባል ተግባር መሆን አለበት፡፡
 
በመሆኑም በአሁኑ ሰአት በአለም አቀፍ ደረጃ የባዮቴክኖሎጂ ሰብሎች (አዝእርቶች) በ2016 የነበረውን 4.7
ሚሊዮን ሄክታር ከነበረው በ2017 189.8 ሚሊዮን ሄክታር በማደግ በ3% ጭማሪ ያለው መሆኑን የ ISSAA
2017 መረጃ ያመለክታል፡፡
በኛ ሃገር ደረጃ ባዮቴክኖሎጂን ባህላዊ በሆነ መንገድ በፈርመንቴሽን መልክ ከቀደምት ዘመናት ጀምሮ ስንገለገል
ይታያል፡፡ ለአብነትን እንጀራ፣ ዳቦ፣ ወተትና የወተት ውጤቶች አጠቃቀም፣ ጠጅ፣ ጠላ ወዘተ. ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እነዚህ
የባዮቴክኖሎጂ ውጤቶችም ኢትዮጵያ ለአለም ያበረከተቻቸው አሰራሮች ጭምር ናቸው፡፡
ጠቅለል አርገን ለማየት ያክል ባዮቴክኖሎጂ ሲባል ሶስት ደረጃዎች አሉት እነሱም የማብላላት፣ ኮንቬክሽናል እና
አድቫንስ ባዮቴክኖሎጂ ናቸው፡፡ ታዲያ ሃገራችን ኢትዮጵያ በየትኛው ደረጃ ላይ ናት ካላችሁ በሁለተኛ ደረጃ ላይ በሚገኘው
ኮንቨክሽናል ባቴክኖሎጂ በምንለው ህዋስን(ሴልን) ቅንጣ ወይም የእጸዋትን አካል(ቲሹ) ቅንጣት ወስዶ የማባዛት
ስራ(ቲሹ ካልቸርን)፤ የተለያዩ የዘረ-መል ማርከሮችን (ዲኤንኤ ማርከር) ቴክኖሎጂን በመጠቀም የዘር መረጣንና
ዘር ማሻሻልን ስራ በመደገፍ እሱን የማፋጠን ስራ የመስራት ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ ከዚህ ባሻገርም ወደ ሶስተኛው ደረጃ
ላይ ለመግባት በበቆሎ ላይ ፕሮጀክት ቀርጻ በእቀባ ሙከራ ላይ ትገኛለች፡፡ በዚህም ረገድ በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር
ኢንስቲትዩት ሁለተኛው ደረጃውንና ሶስተኛው ሙከራ እያደረገ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፣ በጅማ ዩኒቨርስቲ እና
በወሎ ዩኒቨርስቲ ደግሞ ሁለተኛ ደረጃው እየተሰራ ይገኛል፡፡
በዚህ ስራም እስካሁን በቲሹ ካልቸር ደረጃ በሃገራች እንደ ሙዝ፣ እንሰት፣ ሸንኮራ አገዳ፣ አናናስ፣ ቡና፣ ዝንጅብል፣
ድንች ያሉ ሰብሎች ላይ ምርታማነትን ለማሻሻል እና ከተለያዩ ተውሳኮች የጸዳ የመነሻ ዘር(ችግኝ) አባዝቶ ለተጠቃሚ
በማድረስ ለግብርናው ዘርፍ የበኩሉን አስተዋጾ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ከዚህ ባሻገር የእጽዋት ቲሹ ካልቸር ቴክኒክ
በመጠቀም ዝርያቸው በመጥፋት ላይ የሚገኙ ሃገር በቀል እጽዋቶችን ከአደጋ የመከላከል ሰራ እየተሰራ ይገኛል፡፡
በሃገራችን ኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ በባህላዊ መንገድ ስንገለገልበት ብንኖርም ትኩረት ተሰጥቶት ወደ ስራ የተገባው
ከቅርብ ጊዜ ጅምር ነው፡፡ መልዑ በማይባል ደረጃ እንደ ብሄራዊ የእንስሳት ህክምና ኢንስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ ግብርና
ምርምር ኢንስቲትዩት እና አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ያሉ ተቋማት የቀደሙ ሙከራዎች አሉ፡፡ ነገርግን ሁሉንም
የባዮቴክኖሎጂ ዘርፎች ባከተተ መልኩ ራሱን ችሎ የኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት (EBTi) በሚል ሰኔ
1/2008 ዓ.ም የተመሰረተበት የአጭር ጊዜ እንቅስቃሴ እንደሆነ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡
በአሁን ባለው ተጨባጭ እንቅስቃሴ ባዮቴክኖሎጂ 17 ያክል ዩኒቨርስቲዎች በመጀመርያ፣ በሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪ
ተማሪዎች ካሪክለም ተቀርጾ እየተሰጠና ቴክኖሎጂው በጅምር መነቃቃት ላይ የሚገኝ ነው፡፡
ቴክኖሎጂው በቂ ኢንፍራስትራክቸር የሚያስፈልገውና ትኩረትን የሚሻ ከመሆኑ ባሻገር ሃገራችን ኢትዮጵያ ባለ ብዙ
ብዘሃ ሂይወት ሃገር እንደመሆንዋ መጠን በጥንቃቄና ውጤት ሊያሰገኝ በሚችል መልኩ ፈጣንና ቀልጣፋ አሰራርን
ተከትሎ መተግበር ያለበት እንደሆነም ያመላክታል፡፡
በመጨረሻም ኢትዮጵያ የባቴክኖሎጂ ልምድ እንደ ኩባ ካሉ ሃገራት ልምድ ልትወሰድ ይገባል፡፡ ኩባ ለባዮቴክኖሎጂ
የመጀመርያውን ግኝት ያደረገችው ስድስት ሳይንቲስቶችን ወደ ፊንላንድ በመላክ መድሃኒት እንዴት እንደሚመረት
ተምረው እንዲመጡ ተደረገ፡፡ ልምዱን ወስደው ከመጡ በኀላ በሃገራቸው ተመልሰው በ42 ቀናት ውስጥ በቀሰሙት
ትምህርት መሰረት መድሃኒት ሰርተው አመረቱ፡፡ በዚህም ኩባ 80 በመቶ የሚሆነውን የሃገርዋን የመድሃኒት ፍላጎት
የሟሟላት አቅም አላት፡፡ ከዚህ በዘለለም የባዮቴክኖሎጂ ውጤቶች ለተለያዩ ሃገራት ከፍተኛ የገቢ ምንጭ በሚያስገኝ
 
ሁኔታ ታሰራጫለች፡፡ ለአብነትም ለሄፓታይተስ ቢ የሚሆን ክትባት፣ ለመንጋጋ ቆልፍ በሽታ ለመከላከል የሚረዳ ክትባት
ለመጀመርያ ጊዜ ያመረተች ሃገር ናት፡፡
ኩባ በሃገር ውስጥ ካሏት የተለያዩ ተቋማት ጋር እና ከሌሎች አለም አቀፍ ሃገራት ጋር በትብብር
መስራትዋ፣የምታገኘውን የምርምር ውጤት ህብረተሰብ ተኮር በማደረግ ዜጎቿ በቀላሉ አግኝተው እንዲገለገልበት
ማደረጓ፣ የስራውን ሂደቱን ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ በሃላፊነት የሚመራው አንድ አካል መሆኑ እና ለቴክኖሎጂው
ትኩረት መስጠቷ ውጤታማ እንዳደረጋት ይነገራል፡፡
በመሆኑም ሃገራችን ኢትዮጵያ ከእንደዚህ አይነት ሃገራት ተሞክሮን በመውስድ በሰው ሃይል አቅም ግንባታ፣ መሰረተ
ልማትና ኢንፍራስትራክቸር፣ ቤተሙከራዎችን በመገንባትና አስፈላጊ ቁሳቁሶችን አሟልቶ በማደራጀት እንዲሁም ፖሊሲ
እና እስትራቴጅዎችን በቀርጾ ለቴክኖሎጂው ተግባራዊነት ተጅምሮ ከሚታየው በበለጠ ሊሰራ ይገባል፡፡
 
ኢንስቲትዩቱን አስመልክቶ ለሚኖሩ ማናቸውም ጥያቄ አስተያየትና ጥቆማ ጠመንጃ ያዥ ንግድ ባንክ ጎን ባለው ቢሮችን በአካል ወይም ስልክ፡- +251114661867: